የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች...
Wednesday, 21 October 2009
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ኮረም
አለመሙላት ቅሬታ አስነሳ
- ጉባዔው የታገዱትን ሦስት አመራሮች አሰናብቷል
(በፍሬው አበበ)
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ባለፈው እሁድ ባካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በሥራ አስፈፃሚ ግምገማ የታገዱትን ባለሥልጣናት እንዲባረሩ ወሰነ፡፡ የቀድሞ ባለሥልጣናት የምክር ቤቱ ስብሰባ ምልዐተ ጉባዔ (ኮረም) ያላሟላ ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ ም/ቤቱ ግን ይህን ቅሬታ አስተባብሏል፡፡
ም/ቤቱ በዕለቱ ባካሄደው ስብሰባ በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ግምገማ ተካሂዶ ከኃላፊነታቸው የታገዱት የቀድሞ የም/ቤቱ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የልማት ዘርፍ ኃላፊ እገዳ እንዲፀድቅ በማድረግ ሌሎች ሦስት ሰዎች በምትክነት መርጧል፡፡
ስብሰባውን የተከታተሉ የዓይን እማኞች ግን የስብሰባው ጥሪ በጥድፊያ የተላለፈ፣ ምልዐተ ጉባዔ ያላሟላ፣ የታገዱ ሰዎች እንዳይናገሩ የታፈኑበት ነበር በሚል ውሳኔው ሕገወጥ ነው ብለውታል፡፡
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መስከረም 30 ቀን 2002 ባካሄደው የሥራ ግምገማ ላይ "ኃላፊነታቸውን በትክክል አልተወጡም" ያላቸውን ሐጂ ባህር አብደላ - የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት የነበሩ፣ አቶ አማን ኢብራሂም - ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩ፣ አቶ ከድር ራህማቶ - የም/ቤቱ የልማት ዘርፍ ኃላፊ የነበሩትን አግዷል፡፡
በአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት ዋና ፀሐፊ ሐጂ ሁሴን ኑረዲን ፊርማ ጥቅምት 2 ቀን 2002 የተፃፈው ደብዳቤ ኃላፊዎቹ መስከረም 30 ቀን 2002 በተካሄደው ስብሰባ ላይ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በትክክል አለመወጣታቸውን መገምገሙን አስታውሶ ጉዳዩ በጥንቃቄ ተጣርቶ በጠቅላላ ጉባዔ እስኪፀድቅ ከጥቅምት 1 ቀን 2002 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነታቸው እንዲታገዱ መወሰኑን ይገልፃል፡፡ የታገዱት ግለሰቦች በእጃቸው የሚገኙትን ሰነዶች ጥቅምት 2 ቀን 2002 ለም/ቤቱ ፅ/ቤት ተገኝተው እንዲያስረክቡም ደብዳቤው ያዛል፡፡
ከታገዱት አባላት መካከል የም/ቤቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሐጂ ባህር አብደላ ስለጉዳዩ ከሪፖርተር ጋዜጣ ባለፈው ቅዳሜ ዕለት አስተያየት ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ "በደብዳቤው ላይ ኃላፊነታችሁን ባለመወጣታችሁ ይላል፡፡ ምን ኃላፊነት ተሰጥቶን፣ የትኛውን እንዳልተወጣን አይታወቅም፡፡"
"ግምገማው ሲካሄድ በቅድሚያ በግምገማው ነጥቦች ላይ ሳንወያይ፣ ታዛቢ ሆኖ የሚቀመጠው ሰው ማን ይሁን በሚለው ላይ ሳንነጋገር፣ ከኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ም/ቤት ዋና ፀሐፊ ሌላ አንድ ኃላፊ በተገኙበት ግምገማው ተካሂዶ የተላለፈ ውሳኔ ነው፡፡ ግምገማው የአካሄድ ችግር ነበረበት" ብለዋል፡፡
አያይዘውም ም/ቤቱ ኃላፊዎችን ማገድ ይችላል፡፡ ነገር ግን የሚፀድቀው ለጠቅላላ ጉባዔ ቀርቦ ነው፡፡ ጉዳዩ ለጠቅላላ ጉባዔ ቀርቦ የመጨረሻ ውሳኔ ሳያገኝ ንብረት አስረክቡ ማለት ጉዳዩ አስቀድሞ ያለቀለት ያስመስለዋል" ሲሉ ባለፈው ቅዳሜ ዕለት ለሪፖርተር ጋዜጣ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሐጂ ባህር ጨምረውም "ከኃላፊነታችን እንደምንነሳ ከግምገማው በፊት ተወርቶ ሰምተን ነበር ካሉ በኋላ ይህ የግምገማውም አካሄድ አስቀድሞ ዝግጅት የተደረገበት ለመሆኑ በቂ ምስክር ነው" ብለዋል፡፡
ሐጂ ሁሴን ኑረዲን የም/ቤቱ ዋና ፀሐፊ ኃላፊዎቹ ስለታገዱበት ምክንያት ቅዳሜ ዕለት (ጥቅምት 7 ቀን 2002) ተጠይቀው ግምገማ አካሂዶ ኃላፊነታቸውን ባልተወጡት ላይ የእገዳ እርምጃ የወሰደው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ነው፡፡ ይህ የእገዳ ውሳኔ ለጠቅላላ ጉባዔ ቀርቦ መፅደቅ ስላለበት በቅርቡ ጠቅላላ ጉባዔ ለመጥራት በዝግጅት ላይ ነን" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
"የታገዱት ግለሰቦች በጠቅላላ ጉባዔ የመጨረሻ ውሳኔ ሳያገኙ ንብረት አስረክቡ ለምን ተባሉ?" ለተባሉትም "ሰዎቹ ታግደዋል፡፡ በእጃቸው የሚገኙ አንዳንድ ሰነዶች ለሥራ ስለሚያስፈልጉ የተደረገ እንጂ ለሌላ አይደለም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ጥቅምት 8 ቀን 2002 በተጠራው አስቸኳይ ስብሰባው ላይ የተገኙ የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደተናገሩት በም/ቤቱ የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ከእያንዳንዱ ወረዳ ሰባት ያህል ሥራ አስፈፃሚዎች የሚወከሉበት ነበር፡፡ ነገር ግን እሁድ ዕለት በተጠራው ስብሰባ ላይ ከየወረዳው ሦስት ተወካዮች ተመርጠው እንዲገኙ ተደርጓል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ ቢያንስ ከ28 ወረዳዎች 196 ያህል ሰዎች ሊገኙ እንደሚገባ፣ ምልዐተ ጉባዔ ለመሙላት እንኳን 98 ያህል ሰዎች ሊገኙ ይገባል ብለዋል፡፡ ሆኖም የተገኙት ከዚህ በታች የሆኑ ቢሆኑም ስብሰባው እንዲካሄድ መደረጉ ስህተት ነበር በሚል ቅሬታቸውን ተናግረዋል፡፡
ስብሰባውን የመሩት ቀደም ሲል በሥራ አስፈፃሚ ግምገማ ላይ ተገኝተው ትልቅ ሚና የተጫወቱት የኢትዮጵያ እስልምና ጉባዔ ጠቅላይ ም/ቤት ዋና ፀሐፊ መሆናቸውን እማኞቹ አስታውሰው እሁድ ዕለት በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔም እኚሁ ሰው ተገኝተው ሰለእገዳው ከአንድ ሰዓት በላይ ማብራሪያ መስጠታቸውን፣ ሆኖም የታገዱት ሰዎች አንዳቸውም አስተያየት እንዳይሰጡ መደረጋቸውን በማስታወስ ሒደቱ ኢ-ዲሞክራሲያዊና አስቀድሞ የታሰበበት እንደነበር አስረድተዋል፡፡
በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ከታገዱት ሦስት አመራሮች መካከል ሁለቱ መገኘታቸውን እማኞቹ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ሐጂ ሁሴን ኑረዲን ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በየወረዳው መኖር የነበረበት ሥራ አስፈፃሚ ሰባት ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ተመናምኖ ሁለት እና ሦስት የቀረበበት ሁኔታ ነው ያለው ብለዋል፡፡ በተጓደሉት አባላት ምትክ ምርጫ ባለመካሄዱ ምልዐተ-ጉባዔ የሚባለው በሥራ ላይ ያለው ሰው በመሆኑ በስብሰባው ላይ 75 በመቶ ያህል ተገኝቷል፣ ስለሆነም ኮረሙ የተሟላ ነው ብለዋል፡፡
በጉባዔው ላይ "የመናገር ዕድል አልተሰጠንም" የሚለውም ሀሰት ነው ያሉት ሐጂ ሁሴን በተደጋጋሚ እንዲናገሩ ዕድል መስጠቱን፣ ያደራጁዋቸው ሰዎች ሳይቀሩ እንዲናገሩ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ከአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት እንዲሰናበቱ በተደረጉት ሦስት አመራሮች ምትክ በዕለቱ በተካሄደው ጉባዔ ሐጂ በሽር ዳውድ፣ አቶ መካ ፈረጃ እና መምህር ሰይድ መሐመድ መመረጣቸው ዋና ፀሀፊው ጠቁመው እስከ ትላንት ድረስ የሥራ ክፍፍል አለመደረጉን ተናግረዋል፡፡
No comments:
Post a Comment