Thursday, July 30, 2009

BADER

የዘጠነኛው የበድር ጉባኤ የአቋዋም መግለጫ:
በዚህ አመት የኢትዮጵያን ሙስሊሞች የዜግነትና የዕምነት መብት ፈታኝ የሆኑ ዓብይ
መሰናክሎች የተከሠቱበት አመት ሲሆን:
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በሃገርም ይሁን በውጭ የሚኖሩ የዜግነት መብታቸው ለማስከበር
በተለያዩ የትግል ስልት ስሜታቸውን ለመንግስትና ለሃገር ዜጎች ለማስገንዘብ ሞክረዋል::
በድርና ከበድር ጥላ ስር ያሉ ድርጅቶችም የኢትዮጵያን ሙስሊሞች አንድነት መብት እድገትና
ብልጽግና መሠናክል ሊፈጥሩ በሚሞክሩ ፀረ ሰላም ሃይሎችና የሙስሊሞችን የዜግነት
መብታቸውን ለመንፈግ የፈለጉ አንዳንድ የመንግሰት ተቋማት የሚወስዱትን የሃገሪቱን ሕገ
መንግስት ተጻራሪ የሆኑ ተግባሮች እንዲቆሙና:
የኢትዮጵያ መንግስት ለህገ-መንግስቱ መከበር ሃላፊነቱን ወሰዶ ተቋማት የእምነት ነጻነትን
እንዳይጋፉ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እያሳሰበን:
በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የእምነት ነፃነት ላይ ተቋማት የሚወስዱት እርምጃ ፅረ ሕገ-መንግስት
በመሆኑ ሙስሊም ተማሪዎች ያለ ተጽእኖ እምነታቸውንና ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ
እናሳስባለን::
በድር ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከመቼው ጊዜ በበለጠ: በአንድነት በመቆም በሠላማዊና
ህጋዊ በሆኑ መንገዶች ሁሉ መታገል አስፈላጊ መሆኑን በመንገዘብ:
አንድነታችንን አጠናክረን በአገር ውስጥና በውጭ ያለን ሙስሊሞች ልዩነታችንን አቻችለን
በተጠናከረ መልኩ እንድንሰራ ጥሪ እናቀርባለን::
በድር ከመቸውም የበለጠ የሙስሊሞችን ሕብረት በአፅንዖት ተመልክቶ ኮሚኒቲዎች
እንዲደራጁ ለመደገፍ የተደራጁትን በማቀፍ ከሃገር ውስጥና ከአገር ውጭ በተለያዩ አህጉራት
የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን በማስተባበር አንድነትን አጠናክሮ: ለመብት
ለእኩልነት ለእድገትና ብልፅግና በሕብረት ለመስራት በዚህ ጉባኤ በተሃድሶ ተነስቷል::
እንዲሁም የበድር ልዑካን ተልዕኮ በመገምገም:
ሀ) ተልዕኮው የሙስሊሙን የልብ ትርታ የነኩ ጥያቄዎችን ያንፀባረቀ በመሆኑ:
ለ) ጥያቄዎቹን በሃገሪቱ ከፍተኛ ቢሮና በዜና ማሠራጫ ማአከሎች እውቅና በማስገኝቱ:
ሐ) ለሙስሊሙ ህብረተሰብ ድርጅታዊ ስሜት ዕድገትና ስነልቦናዊ ግንዛቤ ስፋት ሰበብ
በመሆኑ:
መ) በድርን በአለኝታነት እንዲታይና የተስፋ ፍንጭ እንዲፈነጥቅ እንዲሁም ሙስሊሞች
እንዲተባበሩ ምክንያት በመሆኑ:
ሠ) ኡለማዎችን በማገናኝትና በማነጋገር ብሎም ተቻችሎ መስራትን በማስቻሉ:
ረ) በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ውጤት በማስገንዘቡ አዎንታዊነቱን አረጋግጦ:
ሆኖም እስካሁን ያልተመለሱ ጥያቄዎቻችን መልስና መፍትሔ እስኪያገኙ ድረስ በድር
ያለማለሳለስ የሚታገል መሆኑን እንገልጻለን::
በተጨማሪ የበድር ፕሬዘደንት በዚህ ዓመት ባደረጉት የሃገር ጉብኝት ከመንግስት
ሚኒስትሮችና ከመጅሊስ ጋር ያደረጉትን ግንኙነት ገምግሞ:
ሀ) መጅሊሱን በማጠናከር በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ዓብይ ጉዳዮች ላይ
ለመመካከርና ለመደጋገፍ በታቻለበት አጋጣሚ ሁሉ አብሮ ለመስራት:
ለ) በሃገራችን ውስጥ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋ ሲደርስ ድጋፍ
በማድረግና በልማት ተግባሮች አብሮ ለመስራት:
ሐ) የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ፌደራላዊና ክልላዊ መዋቅሮች እንዲዳብሩ
የእውቀት ሽግግር ለማድረግ አቅዷል::
እንዲሁም በሙስሊሙ ሕብረተሰብ በኢልማቸውና በሙያቸው ጠቃሚ ስራዎችን የሰሩ
እየሠሩ ያሉና ሠርተው ያለፉ አሊሞቻችን ምሆሮቹን አላህ (ሶ:ወ) ምንዳቸውን
እንዲከፍላቸው ዱአ እያደረግን:
በዚህ ዓመት ያለፉ አሊሞቻችን: ውድ ሐጂ መሃመድ ራፊዕና: ታዋቂው ምሁር
ፕሮፌሰር ሁሴን አህመድ: አላህ (ሱ:ወ) ጀነተል ፈርዶስ እንዲያወርሳቸው
እንለምናለን::
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ለመብትና ለእኩልነት ለሙሉ ዜግነት ተሳትፎ
የሚያደርገውን ትግል ቀጣይና ረጅም መሆኑን በመገንዘብ:
የአገሪቱ ሕገ መንግስት በፈቀደው ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ ሕብረትን አጠናክሮ የሰውና
የንብረት አቋምን በማሳደግ ትግሉን ይቀጥላል::
በድር የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የዜግነት ድርሻቸውን ለአዎንታዊ ለውጥ እንዲሰሩ እያበረታታ
ለመብታቸውና ለእኩልነታቻው የሚያደርጉትን ሕጋዊ እንቅስቃሴ ሁሉ ይደግፋል::
ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን የቦታ መለያየት ሳያግደን በሕብረት በኢማን
በሙስሊማዊነት ፍቅርና ሙሃባ ተከባብረን ተቻችለን እንድንሰራ አላህ (ሱ:ወ) ይርዳን::

No comments: